▫️በሰው ልጆች ረዥም የህይወት ጉዞ ውስጥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚና እንዲ በቀላሉ የሚገለፅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰዎች ወደዚች ምድር ከመጡ አንስቶ አካላዊውን ዓለም ለመግራት የሚያስችሉ የተለያዩ ፈጠራዎችንና የኢኖቬሽን ውጤቶች ያለማቋረጥ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች አለም አሁን ያላትን መልክ ያጎናፀፏት እና የቀጣዩንም ትውልድ እጣ ፋንታ በበጎም ይሁን በክፉ የመወሰን አቅማቸው በእጅጉ የተጠበቀ ነው፡፡ አለማችን እስካሁን ያየቻቸውን የኢኖቬሽን ውጤቶች ለሰው ልጆች ከሰጡት ግልጋሎት እና በታሪክ ውስጥ ካላቸው የገዘፈ ተጽዕኖ አንፃር የሚከተሉት ኢኖቬሽኖች ከምንግዜም ታላላቆቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል እንመልከታቸው፡
▫️1. እሳት (FIRE) - ስለእሳት ስናነሳ ብዙዎች የሚከራከሩበት ጉዳይ ቢኖር እሳት ተፈለሰፈ ከሚባል ይልቅ ተገኝቷል የሚለው ሃሳብ እጅግ ተስማሚ መሆኑን ነው፡፡ ቀደምት የሰው ዘሮች እሳትን እንዴት መፍጠር እና መቆጣጠር እንደሚችሉ ከማወቃቸው በፊት የእሳትን አደጋዎች በየአጋጣሚው ተመልክተው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የእሳትን ምንነት ከተረዱና የሚሰጣቸውን ጥቅም ካወቁ በኋላ እሳትን እንደ አንድ ትልቅ መገልገያ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ አንዳንድ የአርኪዎሎጂ አጥኝዎች እሳት ጥቅም ላይ የዋለው ከ2 ሚሊዮን አመት በፊት ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ 125 ሺ አመታት እንዳስቆጠረ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ክርክር ምንም ተባለ ምንም በሰው ልጆች ታሪክ ታላቅ ግኝት የሆነው እሳት ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ ነገሮች እንዲከላከሉ እና ማብሰል የሚባለውን ትልቅ ክህሎት እንዲረዱ ያስቻል አስገራሚ ግኝት ነው፡፡
▫️2. ተሽከርካሪ ጎማ (WHEEL) - ይህ ፈጠራ የተገኘው በ3500 ዓመተ ዓለም (B.C) በሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን ነበር፡፡ የሜሶፖታሚያ ህዝቦች ይህንን አስገራሚ ፈጠራ የሸክላ ቁሳቁሶችን ለማበጃጀት ሲጠቀሙበት የቆየ ቢሆንም ከሶስትና አራት መቶ አመታት በኋላ ፈጠራው ለሰረገላ ማሽከርከሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የመሳሪያው ተፅዕኖ እጅግ እየናኘ ሄዷል፡፡ ተሽከርካሪ ጎማ ለሰው ልጆች የመጓጓዣ እና የንድግ ስርዓት መፈጠር ትልቅ ሚና ያለው ግኝት ነው፡፡
▫️3. ኦፕቲካል ሌንሶች (OPTICAL LENSES) - የሰዎችን የእይታ አቅም ይበልጥ ለመጨመር እንደ ኦፕቲካል ሌንሶች ያሉ አስገራሚ ግኝቶች እጅግ ወሳኝ ነበሩ፡፡ ረዥም የፈጠራ ሂደት የነበራቸው እነዚህ ግኝቶች በጥንቱ የግብፅ እና የሜሶፖታሚያ የስልጣኔ ዘመን እንደበለፀጉ የሚታመን ሲሆን ከግሪክ የተገኙት የብርሃን ንድፈ ሃሳቦች ደግሞ ለግኝቱ እውን መሆን ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ኦፕቲካል ሌንሶች እንደቴሊቭዥን፣ ፎቶግራፍ እና ፊልም ያሉ ትልልቅ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ መንገድ የጠረጉም ናቸው፡፡
▫️4. ኮምፓስ (COMPASS) - ይህ እንቅስቃሴን ለመምራት የተዘየደው የቴክኖሎጂ ግኝት የሰው ልጆችን የአሰሳ ጥበብና አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ በመወሰድ ተተኪ የማይገኝለት አስገራሚ ግኝት ነው፡፡ የመጀሪያዎቹ ኮምፓሶች በተፈጥሮ የመግነጢሳዊ ይዘት ባላቸው የማዕድን ቁራጮች ወይም (lodestone) አማካኝነት የተሰሩ ሲሆን፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 300 እና 200 አመተ አለም አካባቢ በቻይና እንደተሰሩም ይነገራል፡፡
▫️5. ወረቀት (PAPER) - በ100 ዓመተ አለም አካባቢ በቻይና የተፈለሰፈው ይህ ግኘት የሰው ልጆችን የፅህፈት እና ሃሳብን የማጋራት ልምድ በእጅጉ የቀየረ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ከዚህ ጊዜ በፊት በግብፅ እና በሜክሲኮ የስልጣኔ ዘመናት የተፈለሰፉት እንደ ፓፒረስና አሜት ያሉ የመፃፊያ ቁሶች ለወረቅት መፈጠር አስተዋፅዖ ቢኖራቸውም በቻይና የነበረው ግኝት ግን አሁን ላለው የወረቀት ቴክሎጂ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው፡፡
▫️6. ባሩድ (GUNPOWDER) - ከተለያዩ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች ተቀይጦ የሚሰራው ይህ ተቀጣጣይ ፈንጂ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በቻይና እንደተፈለሰፈ የሚነገር ሲሆን ለዘመናዊው የጦር ቴክኖሎጂ መስፋፋትም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡ ይህ ግኘት በሰው ልጆች የውጊያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑም ይነገርለታል፡፡
▫️7. ማተሚያ (PRINTING PRESS) - እንደአውሮፓውያኑ በ1439 በጀርመናዊው ዮሃንስ ጉተንበርግ የተፈጠረው ይህ መሳሪያ ለሰው ልጆች የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ዘመን ተደርጎ በብዙዎች ይወሰዳል፡፡ ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ በሰዎች እጅ እየተፃፈ የሚሰራጨውን አድካሚ የፅህፈት ስርዓት በሜካናይዝድ ማሽን በመተካት የእውቀት አድማስ በሰዎች ዘንድ በቀላሉ እንዲሰፋፋ እና የሃይማኖት አስተምህሮዎች በአለም ላይ በፍጥነት እንዲናኙ ያስቻለ አስገራሚ ግኘት ነው፡፡
▫️8. ኤሌክትሪክ (ELECTRICITY) - የኤሌክትሪክ ፈጠራ ብዙ ብሩህ አዕምሮዎች ለሺህና ከዚያ በላይ አመታት አስተዋፅዖ ያደረጉበት እፁብ ድንቅ የሆነ የቴክኖሎጂ ግኝት ነው፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ስለኤሌክትሪክ የነበረውን የአለም መረዳት አንድ እርምጃ ያራመደ የመሪነት አበርክቶት እንደነበረው የሚገለፅ ሲሆን በምርምር ዘርፍ ደረጃ ለመስኩ የሰጠው ሁለንተናዊ ትኩረት የቴክኖሎጂውን እድገት በእጅጉ አፋጥኖታል፡፡ ከዚህ ሂደት በማስከተል በ1879 የቶማስ ኤዲሰን የብርሃን አምፖል መፈጠር የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ወደሰዎች እንዲቀርብ ያስቻለ ክስተት ነው፡፡ ይህ የምንግዜም ታላቅ ፈጠራ የሰው ልጆችን የህይወት መንገድ እስከወዲያኘው የቀየረ ግሩም ቴክኖሎጂ ነው፡፡
▫️9. የእንፋሎት ሞተር (STEAM ENGINE) - በስኮትላንዳዊው የፈጠራ ባለሙያ ጀምስ ዋት ከ1763 እስከ 1775 ተሰራ የሚባለው የእንፋሎት ሞተር ሌላኛው ለሰው ልጆች ትልቅ መሰረት የጣለ አስደናቂ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ግኝት በጊዜው ለነበሩት ባቡሮች፣ መርከቦች እና በጠቅላለው ለኢንዱስትሪው አብዮት ዋና የሃይል ምንጭ በመሆን ተከትሎ ለመጣው የሰው ልጅ አብርሆት ታላቅ ውለታ ያደረገ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡
▫️10. የነዳጅ ሞተር (INTERNAL COMBUSTION ENGINE) - በ19ኛው ክፍለዘመን የተዋወቀው ይህ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በመጀመሪያ በቤልጄሚያዊው ኢንጅነር ኢትየን ሌኖየር (በ1859) የተፈጠረ ሲሆን ከጥቂት አመታት በኋላ በጀርመናዊው ኒኮላስ ኦቶ ይበልጥ ሊሻሻል ችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ፈጠራ የኬሚካል ኢነርጂን ወደ ሜካኒካል ኢነርጂ በመቀየር ቀድሞ የእንፋሎት ሞተር ሲሰጥ የነበረውን ግልጋሎት በተሻለ ሁኔታ በመተካት ለዘመናዊ መኪናዎችና አውሮፕላኖች ማገልገል የቻለ አስገራሚ ፈጠራ ነው፡፡
▫️11. ስልክ (TELEPHONE) - የስኮትላንድ ተወላጁ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል በሰው ልጆች የመገናኛ ጥበብ ውስጥ ትልቅ አብዮት የፈጠረውን የስልክ ቴክኖሎጂ በራሱ ስም ያስመዘገበ ታላቅ የፈጠራ ባለሙያ ቢሆንም ከሱ ቀደምና እሱ በነበረበት ዘመንም ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎች ለቴክኖለጂው ማበብ የራሳቸውን አሻራ ጥለዋል፡፡ አሌግዛንደር ግርሃም ቤል አንደአውሮፓውያኑ በ1876 በኤሌክተሪክ ስልክ የመጀመሪያውን ፓትንት ካገኘ በኋላ የሰው ልጆች እርስ በእርስ የመገናኘት ልምድ እስወዲያኛው ተቀይሯል፡፡
▫️12. ክትባት (VACCINATION) - የክትባት ግኘት ለአንዳንዶች አከራካሪ ፈጠራ ቢሆንም ብዙዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ግን በአለም ላይ የተከሰቱ በሽታዎችን በማጥፋት እና የሰው
ልጆችን በመታደግ በኩል እስካሁን ከታዩ አስደናቂ ግኝቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ክትባት እንደአውሮፓውያኑ በ1796 ለፈንጣጣ (smallpox) በሽታ የተሰራው ክትባት ሲሆን ኤድዋርድ ጄነር በተባለ ተመራማሪ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ክትባት በኋላ በ1885 በፈረንዊው ኬሚስትና ባዮለጂስት ሊዩስ ፓስተር የተሰራው የሬቢስ (rabies) ቫይረስ ክትባት ደግሞ ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂ ትልቅ በር የከፈተ ነበር፡፡
▫️13. መኪና (CARS) - ተሽከርካሪ መኪናዎች የሰዎችን የጉዞ ስርዓት እና ተያይዞ የመጣውን የከተሞች ባህሪ እስከወዲያኛው የቀየረ ግሩም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው፡፡ ተሽከርካሪ መኪናዎች በዘመናዊው ቅርፃቸው በአለም ላይ ብቅ ማለት የጀመሩት በ19ነኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አመታት ላይ ሲሆን በዋናነት በጀርመናዊው ካርል ቤንዝ እና ባልደረቦቹ የተከናወኑ ናቸው፡፡ ካርል ቤንዝ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1885 የመጀመሪያዋን ሞተር ብስክሌት ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የመኪና ቴክኖሎጂ በአለም ላይ እየናኘ ሄዷል፡፡
▫️14. አውሮፕላን (AIRPLANE) - በ1903 በአሜሪካውያን ወንድማማቾች ለውጤት የበቃው ይህ አስገራሚ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን የረዥም ርቀት ጉዞ ፈጣን አማራጭ በመስጠት የትራንስፖረት ኢንዱስትሪን እስከወዲያኛው የቀየረ ነው፡፡ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ የአለም ሰዎችን ይበልጥ እንዲቀራረቡ በማድረግ የባህል፣ የምጣኔ ሃብት እና የእውቀት ልውውጦችን ይበልጥ ያዳበረ ቢሆንም በቴክኖሎጂው የማብሰሪያ ጊዚያት በአለም ላይ ለተከሰተው አለምአቀፍ ጦርነት ሌላ አባባሽ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
▫️15. ፔኒሲሊን (PENICILLIN) - እንደአውሮፓውያኑ በ1928 በስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት አሌክዛንደር ፍሌሚንግ የተቀመረው ይህ ግኘት የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን አንድ እርምጃ በማራመድ የመጀመሪያውን አንቲባዮቲክ መድሃኒት ለአለም ያስተዋወቀ ነው፡፡ ፔኒሲሊን እጅግ ብዛት ያላቸው ተላላፊ ባክቴሪያዎችን በመከላከል ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ አንቲባዮቲክ ሲሆን ለዘመናዊው የመድሃኒት ቴክኖሎጂም ፈር ቀዳጅ የሚባል ነው፡፡
▫️16. ሮኬቶች (ROCKETS) - ቀደምት የሚባለው የሮኬት ቴክኖሎጂ ሙከራ በቻይና የስልጣኔ ዘመናት እንደነበር የሚወሱ የታሪክ ማዛግብቶች ቢኖሩም አሁን ላይ የሚታወቀው ዘመናዊ የሮኬት ቴክኖሎጂ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተዋወቀ ነው፡፡ ይህ ግኝት በሰው ልጆች የህዋ ምርምር እና የጠፈር አሰሳ ላይ ትልቅ አበርክቶት የነበረው ፈጠራ ሲሆን በወታደራዊው ዘርፍም የማይናቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡
▫️17. የኒውክለር ማብሊያ (NUCLEAR FISSION) - አተሞችን ይበልጥ ጥቃቅን ወደሆኑ ቅንጣቶች መከፋፈል እና በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ኢነርጂ የመፍጠር ሂደት የኒውክለር ኃይል ማመንጫዎች እና አቶሚክ ቦምቦች እንዲፈጠሩ አስችሏል፡፡ ይህ አስገራሚ ግኘት በ20ኛው ክፍለ ዘመን በዚህ ዘርፍ ዙሪያ ሲሰሩ በነበሩ ስመጥር የፊዝክስ ሊቃውንት የተከናወነ ቢሆንም የኒውክለር ማብሊያውን በዋናነት በመስራት ረገድ ጀርመናውያኑ ኦቶ ሃን እና ፍሪትዝ ስታስመን አንዲሁም የኦስትሪያ ተወላጅ የሆኑት ሊዝ ማይትነር እና ኦቶ ፍሪሲች በቀዳሚነት ይጠቃሳሉ፡፡
▫️18. ሴሚኮንዳክተሮች (SEMICONDUCTOR) - የአሜሪካ ወይም የአለም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማዕከል ከሆነችወ ሲልከን ቫሊ ቅጽል ስም ጀርባ የሚገኘው የሴሚኮንዳክተር ግኘት ብዙ ነገሩ ከሲልከን የተሰራ ሲሆን የአፈጣጠር ሁኔታውም በኤሌክትሪክ ዘመን እና እየመጣ በሚገኘው ዲጂታል ዘመን መካከል ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሴሚኮንዳክተር ቁስን የያዘ መሳሪያ እንደአውሮፓውያኑ በ1947 የተዋወቀ ሲሆን በአሜሪካውያኑ ጆን ባርደን እና ዋልተር ብራታን የተሰራ ነው፡፡
▫️19. የግል ኮምፒውተሮች (PERSONAL COMPUTER) - አንደአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የተፈጠሩት የግል ኮምፒውተሮች የሰው ልጀችን ሁለንተናዊ አቅም በማሳደግ በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ በ1974 በማይክሮ ኢኒስትሩመንቴሽን እና ቴሌሜትሪ ሲስተም (MITS) የመጀመሪያ የሚባለው የግል ኮምፒውተር ከተዋወቀ በኋላ ቀጥለው የመጡት እንደ አፕል፣ ማይክሮሶፍት እና አይ ቢ ኤም ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ዘርፉን እስከወዲያኛው አራቀውታል፡፡
▫️20. በይነ መረብ (INTERNET) - አሁን አሁን የሰው ልጅ እስትንፋስ እስከመሆን የደረሰው ይህ አስገራሚ ግኘት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሙከራዎች ሲደረጉበት የቆየ ቢሆንም አሁን በምናውቀም መልኩ ለሰው ልጆች መድረስ የጀመረው ከ1990ዎቹ ጀምሮ ነው፡፡ በጊዜው አንግሊዛዊው ቲም በርነር-ሊ የመጀመሪያውን የበይነ መረብ መግባቢያ የአለም አቀፍ ድር (WWW) ከቀመረ በኋላ አጠቃላይ የአለም መልክ ሊቀየር ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ንግዳችን፣ ፖለቲካችን፣ መዘናኛችን የፈለጋችሁን ስም ስጡት ብቻ ሁለ ነገራችን በኢንተርኔት እና በኢንተርኔት ሁኗል፡፡
https://t.me/SSWSIT